عربيEnglish

The Noble Qur'an Encyclopedia

Towards providing reliable exegeses and translations of the meanings of the Noble Qur'an in the world languages

The Romans [Ar-Room] - Amharic Translation - Africa Academy

Surah The Romans [Ar-Room] Ayah 60 Location Maccah Number 30

አሊፍ፤ ላም፤ ሚይም።

ሩም (በፋርሶች) ተሸነፈች።

በጣም (ለዐረቡ ዓለም) ቅርብ በሆነችው ምድር ላይ እነርሱም (ከሶስት አመት ያላነሰ ከዘጠኝ ባልበለጠ በጥቂት አመታት ውስጥ) ከመሸነፋቸው በኋላ ያሸንፋሉ።

(ከሶስት አመት ያላነሰ ከዘጠኝ ባልበለጠ) በጥቂት አመታት ውስጥ (ያሸንፋሉ)። ጉዳዩ በፊትም ሆነ በኋላ የአላህ ነውና። በዚያ ቀንም ምዕምናን ይደሰታሉ።

በአላህ እርዳታ (ይደሰታሉ)። አላህ የሚሻውን ሰው ይረዳል። እርሱም ሁሉን አሸናፊና አዛኝ ነው።

አላህ እርዳታን በቁርጥ ቀጠረ። አላህ ቀጠሮውን አያፈርስም። ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።

ከቅርቢቱ ህይወት ግልጹን ብቻ ያውቃሉ። እነርሱም ከኋለኛይቱ ዓለም ፍጹም ዘንጊዎች ናቸው።

በነፍሶቻቸው ሁኔታ አያስተውሉምን ? ሰማያትን፤ ምድርንና በመካከላቸው ያለውን ሁሉ በእውነትና በተወሰነ ጊዜ እንጂ አልፈጠራቸዉም። ከሰዎች መካከል ብዙዎቹ ከጌታቸው ጋር በመገናኘት በእርግጥ ከሓዲያን ናቸው።

በምድር ላይ አይሄዱምና የእነዚያን ከበፊታቸው የነበሩትን ሰዎች ፍፃሜ እንዴት እንደነበር አይመለከቱምን? በኃይል ከእነርሱ ይበልጡ ነበሩ። ምድርንም አረሱ። እነዚህ ከአለሟትም የበለጠ አለሟት። መልዕክተኞቻቸዉም በተአምራቶች መጡባቸው። (ግና አስተባበሉና ጠፉ።) አላህም የሚበድላቸው አልነበረም። ግና ነፍሶቻቸውን በራሳቸው ይበድሉ ነበር።

ከዚያም የእነዚያ ያጠፉት ሰዎች መጨረሻ በአላህ አናቅጽ በማስተባበላቸውና በእርሷ ይሳለቁ በመሆናቸው ምክንያት እጅግ መጥፎዋ (ቅጣት) ሆነ።

አላህ መፍጠርን ይጀምራል። ከዚያም ይመልሰዋል። ከዚያም ወደ እርሱ ትመለሳለችሁ።

ሰዓቲቱም በምትከሰትበት ቀን አመጸኞች ጭጭ ይላሉ (ተስፋ ይቆርጣሉ)።

ለእነርሱም ከሚያጋሯቸው ጣዖታት መካከል አማላጆች አይኖሩዋቸዉም። በሚያጋሯቸዉም ጣዖታት ከሓዲያን ይሆናሉ።

ሰዓቲቱም በምትከሰትበት ቀን በዚያ ቀን ይለያያሉ።

እነዚያ በአላህ ያመኑትና መልካሞችን ስራዎች የሰሩትማ እነርሱ በገነት ጨፌ ውስጥ ይደሰታሉ።

እነዚያም በአላህ የካዱትማ በአናቅጻችንና በኋለኛይቱም ዓለም መገናኘት ያስተባበሉት እነዚያ በቅጣት ውስጥ የሚጣዱ ናቸው።

አላህንም በምታመሹና በምታነጉም ጊዜ አጥሩት።

ምስጋናም በሰማያትና በምድር ውስጥ ለእርሱ ብቻ የተገባው ነው። በሰርክም በቀትር ውስጥ በምትገቡም ጊዜ አጥሩት።

ህያውን ከሙት ያወጣል። ሙትንም ከህያው ያወጣል። ምድርንም ከሞተች በኋላ ህያው ያደርጋታል። ልክ እንደዚሁም (ከመቃብር) ትወጣላችሁ።

እናንተንም ከአፈር መፍጠሩ ከዚያም እናንተ ወዲያውኑ የምትበታተኑ ሰዎች መሆናችሁ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው።

ለእናንተም ከነፍሶቻችሁ ሚስቶችን ወደ እነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ህዝቦች ሁሉ አያሌ ተዐምራት አሉበት።

ሰማያትንና ምድርን መፍጠሩ የቋንቋዎቻችሁና የመልኮቻችሁም መለያየት ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለአዋቂዎች አያሌ ታዐምራት አሉበት።

በሌሊትም ሆነ በቀን መተኛታችሁ ከችሮታዉም መፈለጋችሁም ከምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለሚሰሙ ህዝቦች ሁሉ ብዙ ታዐምራት አሉበት።

ብልጭታንም ፈሪዎችና ከጃዮች ስትሆኑ ለእናንተ ማሳየቱ ከሰማይም ውሃን ማውረዱ በእርሱም ምድርን ከሞተች በኋላ ህያው ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው። በዚህ ውስጥ ለሚያስቡ ህዝቦች ሁሉ አያሌ ታዐምራት አሉበት።

ሰማይና ምድርም (ያለ ምሰሶ) በትእዛዙ መቆማቸው ከዚያም (በመልአኩ ንፋት) ለትንሳኤ ከምድር ጥሪን በጠራችሁ ጊዜ እናንተ ወዲያውኑ የምትወጡ መሆናችሁ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው።

በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ የእርሱ ብቻ ነው። ሁሉም ለእርሱ ታዛዦች ናቸው።

እርሱ ያ ፍጡራንን ከምንም የሚጀምር (የሚያስገኝ) ከዚያም የሚመልሳቸው ብቸኛ አምላክ ነው። መመለሱም በእርሱ ላይ በጣም ቀላል ነው። ለእርሱም በሰማያትና በምድር ከፍተኛው ምሳሌ (ባህሪ) አለው። እርሱም ሁሉን አሸናፊና ጥበበኛ ነው።

(ጣዖት አምላኪዎች ሆይ!) ለእናንተ ከነፍሶቻችሁ የሆነን ምሳሌ አደረገላችሁ። እርሱም እጆቻችሁ ከያዟቸው ባሮች ውስጥ በሰጠናችሁ ጸጋ ለእናንተ ተጋሪዎች አሏችሁን? ታዲያ እናንተና እነርሱ በእርሱ እኩል ለእኩል (ትክክል) ናችሁን? ነፍሶቻችሁን (ብጤዎቻችሁን) እንደምትፈሩ ትፈሯቸዋላችሁን ? ልክ እንደዚሁ ለሚያስተውሉ ህዝቦች ሁሉ አናቅጽን እንገልጻለን።

ይልቁንም እነዚህ የበደሉ ሰዎች ያለ ዕውቀት ዝንባሌዎቻቸውን ተከተሉ። አላህም ያጠመመውን ሰው የሚያቀናው ማነው? ለእነርሱም ከረዳቶች ምንም የላቸዉም።

(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ወደ እውነት ተዘንባይ ሆነህም ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ። የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በርሷ ላይ የፈጠረባትን ሃይማኖት (ያዟት)። የአላህን ፍጥረት መለወጥ የለም። ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው። ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም።

ወደ እርሱ ተመላሾች ሆናችሁ የአላህን ሃይማኖት ያዙ። ፍሩትም። ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ። ከአጋሪዎችም አትሁኑ።

ከእነዚያ ሃይማኖታቸውን ከለያዩትና ክፍልፍልም ከሆኑት አትሁኑ። ቡድን ሁሉ እነርሱ ዘንድ ባለው ነገር ብቻ ተደሳቾች ናቸው።

ሰዎችንም ችግር ባገኛቸው ጊዜ ጌታቸውን ወደ እርሱ ተመላሾች ሆነው ይጠሩታል። ከዚያም ከእርሱ ችሮታንም ባቀመሳቸው ጊዜ ከእነርሱ ከፊሎቹ ወዲያውኑ በጌታቸው ጣዖትን ያጋራሉ።

በሰጠናቸው ጸጋ ሊክዱ (ያጋራሉ)። ተጣቀሙም። በእርግጥም መጨረሻችሁን ወደፊት ታውቃላችሁ።

በእነርሱ ላይ አላህ አስረጅን አወረደን? ታድያ እርሱ በነዚያ በእርሱ ያጋሩ በነበሩት ነገር ይናገራልን? የለም።

ሰዎችንም ችሮታን ባቀመስናቸው ጊዜ በእርሷ ይደሰታሉ። እጆቻቸዉም ባሳለፉት ምክንያት መከራ ብታገኛቸው ወዲያውኑ እነርሱ ተስፋ ይቆርጣሉ።

አላህ ለሚሻው ሰው ሲሳይን የሚያሰፋ የሚያጠብም መሆኑን አያዩምን? በዚህ ውስጥ ለሚያምኑ ህዝቦች አስደናቂ ምልክቶች አሉበት።

ስለዚህ (አማኝ ሆይ!) የዝምድናን ባለቤት ተገቢውን ስጠው። ለድሃም ለመንገደኛም እርዳ። ይህ ለእነዚያ የአላህን ፊት ለሚሹ ሁሉ መልካም ነው። እነዚያ እነርሱም በሁለተኛው ዓለም የፈለጉትን የሚያገኙ ምርጥ ክፍሎች ናቸው።

(ሰዎች ሆይ!) በሰዎች ገንዘቦች ውስጥም ይጨመር ዘንድ በማቀድ የምትሰጡት ገንዘብ በአላህ ዘንድ ቅንጣት አይጨምርም። የአላህን ፊት ብቻ የምትሹ ሆናችሁ የምትሰጡት ምጽዋት ግን እነዚያ (እውነተኛ ሰጪዎች) (ምንዳቸው) የተነባበረላቸው እነርሱ ናቸው።

አላህ ያ የፈጠራችሁ ከዚያም ሲሳይን የሰጣችሁ ከዚያም የሚገድላችሁ ከዚያም ህያው የሚያደርጋችሁ ነው። ከምታጋሯቸው ጣዖታት ውስጥ ከዚህ ሁሉ አንዳችን የሚሰራ አለን? ለአላህ ጥራት ይገባው በእርሱ ከሚያጋሩትም ሁሉ ላቀ።

የሰዎች እጆች በሰሩት ኃጢአት ምክንያት የዚያን የሰሩትን ከፊሉን ያቀምሳቸው ዘንድ መከራው በየብስና በባህር ተገለጠ (ተሰራጨ)። እነርሱ ሊመለሱ ይከጀላልና።

(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) «በምድር ላይ ሂዱ የእነዚያንም በፊት የነበሩት ሰዎች መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከቱ።» በላቸው። አብዛኞቻቸው አጋሪዎች ነበሩ።

(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ለእርሱ መመለስ የሌለው ቀን የትንሳኤ ቀን ከአላህ ሳይመጣ በፊት ፊትህን ወደ ቀጥተኛው ሃይማኖት ቀጥ አድርግ ። በዚያ ቀን ወደ ገነትና ወደ እሳት ይለያያሉ።

በአላህ የካደ ሰው የክህደቱ ጠንቁ በእርሱው ላይ ብቻ ነው። መልካምም የሰሩ ሁሉ ለነፍሶቻቸው ማረፊያዎችን ያዘጋጃሉ።

እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችንም የሰሩትን ከችሮታው ይመነዳ ዘንድ (ይለያያሉ)። እርሱ ከሓዲያንን አይወድምና።

(ሰዎች ሆይ!) ንፋሶችንም (በዝናብ) ልታበስራችሁ ከችሮታዉም (በእርሷ) ሊያቀምሳችሁ መርከቦችም በትእዛዙ እንዲንሻለሉ ከችሮታዉም እንድትፈልጉ ታመሰግኑትም ዘንድ መላኩ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው።

(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ካንተ በፊትም መልዕክተኞችን ወደ ህዝቦቻቸው በእርግጥ ላክን። በግልጽ ማስረጃዎችም መጡባቸው። ከእነዚያ ካመጹትም ተበቀልን። ምዕመናኖችንም መርዳት በእኛ ላይ ተገቢ ሆነ።

አላህ ያ ! ንፋሶችን የሚልክ ነው። (ንፋሶቹም) ደመናን ይቀሰቅሳሉ። በሰማይ ላይም እንደሚሻ ይዘረጋዋል ። ቁርጥራጮችም ያደርገዋል። ዝናቡንም ከደመናው መካከል ሲወጣ ታያለህ። በእርሱም ከባሮቹ የሚሻውን በለየ ጊዜ ወዲያውኑ እነርሱ ይደሰታሉ።

በእነርሱም ላይ ከመውረዱ በፊት ከእርሱ በፊት በእርግጥ ተስፋ ቆራጮች ነበሩ።

ምድርንም ከሞተች በኋላ እንዴት ህያው እንደሚያደርጋት ወደ አላህ ችሮታ ፈለጎች ተመልከት። ይህን አድራጊ ጌታ ሙታንንም በእርግጥ ህያው አድራጊ ነው ። እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና።

ንፋስንም በአዝመራዎች ላይ ብንልክና ገርጥቶ ቢያዩት ከእርሱ በኋላ በእርግጥ ችሮታውን የሚክዱ ይሆናሉ።

(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አንተም ሙታንን አታሰማም። ደንቆሮዎችንም ዟሪዎች ሆነው በሸሹ ጊዜ ጥሪን አታሰማም።

(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) አንተ እውሮችንም ከጥመታቸው የምታቀና አይደለህም። በአናቅጻችን የሚያምኑትን ሰዎች እንጂ ሌላን አታሰማም። እነርሱም ታዛዦች ናቸው።

(ሰዎች ሆይ!) አላህ ያ ከደካማ ፍትወት ጠብታ የፈጠራችሁ ነው። ከዚያ ከደካማነት በኋላም ኃይልን አደረገ። ከዚያም ከብርቱነት በኋላ ደካማነትና ሽበትንም አደረገ። የሚሻውን ይፈጥራል። እርሱም ሁሉን አዋቂውና ቻዩ ነው።

ሰዓቲቱ በምትከሰትበት ቀን ከሓዲያን «ከአንዲት ሰዓት በስተቀር በመቃብር (በዱንያ) አልቆየንም።» ብለው ይምላሉ። ልክ እንደዚሁ በዚህኛው ዐለምም እያሉ ከእውነት ይመለሱ ነበር።

እነዚያም እውቀትንና እምነትን የተሰጡት «በአላህ መጽሐፍ ፍርድ እስከ ትንሳኤ ቀን በእርግጥ ቆያችሁ ይህም የካዳችሁት የትንሳኤ ቀን ነው። ግን እናንተ የማታውቁ ነበራችሁ።» ይሏቸዋል።

በዚያም ቀን እነዚያን የበደሉትን ማመካኘታቸው አይጠቅማቸዉም። እነርሱም በወቀሳ አይታለፉም።

በዚህም ቁርኣን ውስጥ ለሰዎች የምሳሌ አይነቶችን ሁሉ በእርግጥ ገለጽን። ተዓምርን ብታመጣላቸው እንኳን እነዚያ በአላህ የካዱት ሰዎች «እናንተ አበላሺዎች የጥፋት ተጣሪዎች እንጂ ሌላ አይደላችሁም።» ይላሉ።

ልክ እንደዚሁ አላህ በነዚያ በማያውቁት ሰዎች ልቦች ላይ ያትማል።

(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) ስለዚህ ታገሥ። የአላህ ቀጠሮ እውነት ነውና። እነዚያም በትንሳኤ የማያረጋግጡት ሰዎች አያቅልሉህ።