The Noble Qur'an Encyclopedia
Towards providing reliable exegeses and translations of the meanings of the Noble Qur'an in the world languagesMutual Disillusion [At-Taghabun] - Amharic Translation - Africa Academy
Surah Mutual Disillusion [At-Taghabun] Ayah 18 Location Madanah Number 64
በሰማያት ውስጥም ሆነ በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ አላህን ያሞግሳል። ንግስናው የእርሱ ብቻ ነው። ምስጋናም ለእርሱ ብቻ ነው። እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው።
እርሱ ያ የፈጠራችሁ ነው። ከእናንተም መካከል ከሓዲ አለ። ከእናንተም መካከል አማኝ አለ። አላህ የምትሰሩትን ሁሉ ተመልካች ነው።
(እርሱ) ሰማያትንና ምድርን በእውነት ፈጠረ። ቀረጻችሁም ቅርጻችሁንም አሳመረ። መመለሻችሁም ወደ እርሱ ብቻ ነው።
በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለውን ሁሉ ያውቃል። የምትደብቁትንም ሆነ የምትገልጡትን ያውቃል። አላህም በልቦች ውስጥ ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነው።
የእነዚያ ከአሁን በፊት የካዱትና የክህደታቸውን ቅጣት የቀመሱ ህዝቦች ወሬ አልመጣላችሁምን? ለእነርሱ አሳማሚ ቅጣት አለባቸው።
ይህ (ቅጣት) እነርሱ መልዕክተኞቻቸው አስረጂዎችን ይዘው ሲመጡላቸው «ሰዎች ይመሩናልን?» ስላሉና ስለ ካዱ፤ ከእምነትም ስለ ዞሩ ነው። አላህ ከእነርሱ እምነት ተብቃቃ። አላህ ተብቃቂና ምስጉን ነውና።
(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) እነዚያ በአላህ የካዱት ሰዎች በፍጹም የማይቀሰቀሱ መሆናቸውን አሰቡ። «(እንዴት አትቀሰቀሱም?) በጌታየ ይሁንብኝ ትቀሰቀሳላችሁ። ከዚያ ትፈጽሙት የነበረውን ተግባራችሁን ትነገራላችሁ። ይህ ተግባር ለአላህ ቀላል ነው» በላቸው።
በአላህ በመልዕክተኛውና በዚያም ባወረድነው ብርሃን እመኑም። አላህ የምትሰሩትን ሁሉ ውስጠ አዋቂ ነውና።
(ይኸዉም) ለመሰብሰቢያው ቀን የሚሰበስባችሁ እለት አስታውሱ። ይህ ቀን የቁጭት ቀን ነው። በአላህም የሚያምን ሰው መልካምንም የሚሠራ ከርሱ ኃጢአቶቹን ይሰርይለታል፤ (ይፍቅለታል)፤ ከስሮቿ ወንዞች የሚፈሱባት ገነቶች ለዘላለም ያስገባዋል። ይህ ታላቅ እደለኝነት ነው።
እነዚያም የካዱትና በአንቀፆቻችንም ያስተባበሉት የዝንታለም እሳት ባለቤቶች ማለት እነርሱ ናቸው። (ጀሀነም) መመለሻነቷ ምን ይከፋ!
ከመከራም በአላህ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ማንንም አይነካም። በአላህ የሚያምን ሰው አላህ ልቡን (ለትዕግስት) ይመራለታል። አላህም በሁሉም ነገር አዋቂ ነው።
አላህን ታዘዙ መልዕክተኛውንም ታዘዙ። ብትዞሩም (መልዕክተኛውን አትጎዱም።) በመልዕክተኛችንም ላይ ያለበት በግልጽ ማድረስ ብቻ ነው።
አላህ ከእርሱ በስተቀር ትክክለኛ አምላክ የለም። ትክክለኛ አማኞች በአላህ ብቻ ይመኩ።
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከሚስቶቻችሁና ከልጆቻችሁ (ከአላህ መንገድ በማስተጓጎል) ለእናንተ ጠላቶች የሆኑ አሉ። ስለዚህ ተጠንቀቋቸው። ይቅርታ ብታደርጉ፤ ብታልፏቸዉም፤ ብትምሩዋቸዉም፤ አላህ በጣም መሀሪ፤ አዛኝ ነው።
ገንዘቦቻችሁና ልጆቻችሁ ለእናንተ መፈተኛ ብቻ ናቸው። አላህም ከእርሱ ዘንድ ታላቅ ምንዳ አለ።
አላህንም የቻላችሁትን ያህል ፍሩት። ትዕዛዙን ስሙም፤ ታዘዙም፤ ለግሱም፤ ለነፍሶቻችሁ መልካምን ይሰጣችኋልና። የነፍሶቻቸዉን ንፍገት የሚጠበቁ ሰዎች ሁሉ እነዚያ እነርሱ ፍላጎታቸውን የሚያገኙ ናቸው።
ለአላህ መልካም ብድርን ብታበድሩት (ምንዳውን) ለእናንተ ይደራርበዋል። ለእናንተም ይምራል። አላህ አመስጋኝና ታጋሽ ነውና።
(እርሱ) ስውሩንም ይፋዉንም ሁሉን አዋቂ ኃያልና ጥበበኛ ነዉና።

