عربيEnglish

The Noble Qur'an Encyclopedia

Towards providing reliable exegeses and translations of the meanings of the Noble Qur'an in the world languages

Those who drag forth [An-Naziat] - Amharic Translation - Africa Academy

Surah Those who drag forth [An-Naziat] Ayah 46 Location Maccah Number 79

(ነፍስን (ሩህን)) በኃይል መንጫቂዎች በሆኑት፤

በቀስታ መምዘዝን መዛዦች በሆኑትም፤

መዋኘትንም ዋኚዎች በሆኑት፤

መቅደምንም ቀዳሚዎች በሆኑት፤

ጉዳይንም አስተናባሪዎች በሆኑት መላዕክት እምላለሁ (በእርግጥ ትቀሰቀሳላችሁ)።

(ይህም የሚሆነው) ተርገፍጋፊይቱ (ምድር) በምትርገፈገፍበት ቀን፤

ተከታይቱም በምትከተላት ቀን (ትቀሰቀሳላችሁ)።

በዚያ ቀን ልቦች ተሸባሪዎች ናቸው።

ዓይኖቻቸው ተዋራጆች (አቀርቃሪዎች) ናቸው።

«እኛ ወደ መጀመሪያይቱ ሁኔታ ተመላሾች ነን እንዴ?» ይላሉ።

የበሰበሱ አጥንቶች በሆንን ጊዜ እንደገና እንቀሰቀሳለን?

«እንዲያማ ከሆነ ያች የኪሳራ መመለስ ናታ!» ይላሉ።

እርሷን (እውን የምታደርጋት) አንዲት ጩኸት ብቻ ናት።

ወዲያውኑ (ከቀብራቸው ወጥተው) በምድር ገጽ ላይ ናቸው።

(መልዕክተኛችን ሙሐመድ ሆይ!) የሙሳ ወሬ መጣልህን?

ወደ ፈርዖን ሂድ፤ ወሰን አልፏልና።

(እንዲህም) በለው: «እራስህን ለማጥራት ታስባለህን?

ጌታህንም ትፈራ ዘንድ መንገዱን ልመራህ፤ (ታስባለህን?)»

(ሙሳ ለፈርዖን) ታላቁንም ተዐምር አሳየው።

አስተባበለም፤ አመጸም፤

ከዚያም (በምድር ላይ) ለማጥፋት የሚተጋ ሆኖ ዞረ።

(ህዝቡን) ሰበሰበም ተጣራም።

«እኔ ከሁሉ በላይ የሆንኩት ጌታችሁ ነኝ» አለም።

አላህም በመጨረሻይቱና በፊተኛይቱ (ዓለም) ቅጣት ያዘው።

በዚህ ውስጥ አላህን ለሚፈሩ በእርግጥ ማስጠንቀቂያ አለበት።

በአፈጣጠር እናንተ ይበልጥ የበረታችሁ ናችሁን? ወይስ ሰማይ? (አላህ) ገነባት።

ከፍታዋን አጓነ አስተካከላትም።

ሌሊቷንም አጨለመ፤ ቀኗንም ግልጽ አደረገ።

ጋራዎችንም አደላደላቸው።

ለእናንተም ለእንስሶቻችሁም መጣቀሚያ ይሆን ዘንድ (ይሄን አደረገ)።

ሰው ሁሉ የሰራውን የሚያስታውስበት ቀን፤

ገሀነምም ለሚያይ ሰው በተገለጠች ጊዜ፤

ወሰን ያለፈ ሰውማ፤

ቅርቢቱንም ሕይወት የመረጠ፤

በእርግጥ መኖሪያው ጀሀነም ናት።

በጌታው ፊት መቆምን የፈራና ነፍሱንም ከዝንባሌዋ የከለከለማ፤

በእርግጥ መኖሪያው ገነት ናት።

ስለሰዓቲቱም መቼ እንደምትከሰት ይጠይቁሃል።

(ለመሆኑ አንተ ስለዚያች እለት) በመወሳቷ ምን ላይ አለህበትና?

የእርሷ ጉዳይ የሚመለሰው ወደ ጌታህ ብቻ ነው።

አንተ ያለብህ ለሚፈራት ሰው ሁሉ ስለ እርሷ (ከወዲሁ) ማስጠንቀቅ ነው።

እነርሱ የሚያዩዋት ቀን የአንዲትን ቀን ምሽት ወይም ረፋዷን እንጂ ያልቆዩ ይመስላሉ።